A- A A+

english

ፕሮፋይል

User Rating: 0 / 5

Star InactiveStar InactiveStar InactiveStar InactiveStar Inactive
 

የኢትዮጵያ ብሮድካስት ባለሥልጣን አጠቃላይ ሁኔታ

የኢትዮጵያ ብሮድካስት ባለሥልጣን በአዋጅ ቁጥር 178/91 (533/99 እንደ ተሻሻለው) የተቋቋመ የፌዴራል መንግሥት /ቤት ነው፡፡ የመንግሥት ኮሙኒኬሽንን ጉዳዮች /ቤትን ለማቋቋም በወጣው አዋጅ 158/2001 አንቀጽ 11 መሠረት የሕትመት ሬጉላቶሪ ስልጣን ተሰጥቶታል፡፡

በዚህም ከአንድ ክልል በላይ ለሚሰራጩ የሕትመት ሥራዎች የምዝገባ የምስክር ወረቀት ይሰጣል፡፡ በተጨማሪ በንግድ ምዝገባ እና ፈቃድ አዋጅ ቁጥር 686/2002 መሠረት 9 የመገናኛ ብዙኃንና ተያያዥ የንግድ ሥራ መደቦች ላይ የሙያ ብቃት ማረጋገጫ ይሰጣል፡፡

ከዚህም ባሻገር በማስታወቂያ አዋጅ ቁጥር 759/2004 መሠረት የማስታወቂያ ሥራ ላይ መሰማራት ለሚፈልጉ አካላት ብቃት ማረጋገጫ ይሰጣል፡፡ ተጠሪነቱም ለኢፌዴሪ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሲሆን ቦርድ፣ ዋና ዳይሬክተር፣ /ዋና ዳይሬክተር፣ 14 ዳይሬክቶሬቶች፣ እና አስፈላጊ ሠራተኞች አሉት፡፡ የባለሥልጣን /ቤቱ ዋና ዓላማ ለፖለቲካዊ፣ ለማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ዕድገት አስተዋጽኦ የሚያደርግ ጥራቱ የተጠበቀ ቀልጣፋና አስተማማኝ የመገናኛ ብዙኃን እንዲስፋፋ ማድረግ እንዲሁም የክትትልና የሱፐርቪዥን ሥራዎችን በማከናወን የዓቅም ግንባታ ድጋፎችን መስጠት ነው፡፡

የባለሥልጣኑ ዋና ዋና ተግባርና ኃላፊነቶች የመገናኛ ብዙሃን ለማኅበራዊ፣ ለፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ እድገት አስተዋጽኦ በሚያበረክት ሁኔታ መካሄዱን ማረጋገጥ፣ ለብሮድካስት አገልግሎት የተመደበውን ሬዲዮ ሞገድ ማቀድ፣ መመደብ፣ ማስተዳደር፣ ለብሮድካስት አገልግሎት ፈቃድ መስጠት፣ ህገ - ወጥ ስርጭትን መቆጣጠር፣ ከአንድ ክልል በላይ የሚሰራጩ በየጊዜው የሚወጡ ህትመቶች (ጋዜጣና መፅሔት) መመዝገብ፣ በመገናኛ ብዙሃንና ተያያዥ የንግድ ሥራዎች ለመሰማራት ለሚፈልጉ አካላት የብቃት ማረጋገጫ ሰርተፍኬት መስጠት፣ በማስታወቂያ ሥራ ለመሠማራት የሚፈልጉ አካላት የብቃት ማረጋገጫ ምስክር ወረቀት መስጠት፣ የብሮድካስት አገልግሎት መሳሪያዎች ስታንዳርድ መወሰን፣ የብሮድካስት ጣቢያ የሚቋቋምበትን ሥፍራ መወሰን፣ ለዘርፉ መስፋፋትና ዕድገት የሚያግዙ ጥናቶች ማካሄድ፣ ዘርፉን የሚመለከቱ መረጃዎችን አጠናቅሮና አደራጅቶ መያዝ፣ በሬዲዮና ቴሌቪዥን በሚተላለፉ ዜናዎች፣ ፕሮግራሞችና ማስታዎቂዎች ላይ ከህብረተሰቡ ለሚቀርቡ ቅሬታዎችና ጥቆማዎች አጣርቶ ውሳኔ መስጠት እና በምርጫ ወቅት ከተወዳዳሪ የፖለቲካ ፓርቲዎችና ከምርጫ ቦርድ ጋር በመሆን ነፃ የአየር ሰዓትና የጋዜጣ አምድ መመደብ ናቸው፡፡

ባለስልጣኑ በአዋጅ የተሰጡትን ተግባርና ኃላፊነቶች በሚፈለገው አግባብ ተግባራዊ ለማድረግ የመሠረታዊ የአሰራር ሂደት ለውጥ ጥናት በማከናወን ሙሉ ትግበራ ውስጥ የሚገኝ ተቋም ነው፡፡ በአሁኑ ወቅት የውጤት ተኮር ሥርዓት እየተገበረ የሚገኝ ሲሆን የውጤት ተኮር ምዘናን ተግባራዊ ማድረግ ጀምሯል፡፡

ባለሥልጣን /ቤቱ ከተቋቋመ በኃላ የሬዲዮ ሞገድ እቅድ በማዘጋጀት፣ የፈቃድ አሰራር ስርዓት በመዘርጋት የብሮድካስት አገልግሎት ፈቃድ እየሰጠ ይገኛል፡፡ በዚህ መሠረት ባለሥልጣን መሥሪያ ቤቱ ከመቋቋመ በፊት የነበረውን በፌዴራል ደረጃ የሚገኘውን የኢትዮጵያ ብሮድካስት ኮርፖሬሽን ሳይጨምር 7 የክልል መንግሥት እና 2 የከተማ መስተዳደር የህዝብ ሬዲዮ ፈቃድ መስጠቱ፣ 13 ሬዲዮ እና 20 የሳተላይት ቴሌቭዥን የንግድ እና 49 ማኅበረሰብ ሬዲዮ ብሮድካስት አገልግሎቶች፣ 3 የክልል መንግሥታት እና 2 የከተማ መስተዳደር የቴሌቪዥን ብሮድካስት አገልግሎቶች እንዲሁም የውጭ ፕሮግራሞችን ተቀብሎ ለደንበኞች ለሚያደርስ አንድ ድርጅት ፈቃድ ሰጥቷል፡፡

የሕትመት ውጤቶችን በሚመለከት በፌደራል ደረጃ ከሚዘጋጁ ጋዜጦችና መጽሔቶች በተጨማሪ ክልሎች የራሳቸውን ሕትመቶች እያዘጋጁ ያሰራጫሉ፡፡ ከአንድ ክልል በላይ ለሚሰራጩና በየጊዜው ለሚወጡ በርካታ የግል ሕትመቶች (ጋዜጣና መጽሔት) የምዝገባ ምስክር ወረቀት ሰጥቷል።

በዘመናዊ የብሮድካስት አገልግሎት መሣሪያ በመታገዝ የፕሮግራም ሞኒተሪንግ ሥራ እየሠራ ይገኛል፡፡ ለብሮድካስት አገልግሎት ባለሙያዎች የተለያዩ የአቅም ግንባታ ሥራዎች መሠራታቸው እና በምርጫ ወቅት ለተወዳዳሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች  ነጻ የአየር ጊዜና የጋዜጣ አምድ ምደባ በተሳካ ሁኔታ ማካሄዱ እንዲሁም የሲቪል ሰርቪስ ሪፎርም በመ/ቤቱ ተግባራዊ እንዲሆን መደረጉ መስሪያ ቤቱ እያከናወናቸው ከሚገኙ አበረታች ሥራዎች መካከል ይጠቀሳሉ፡፡

ባለስልጣኑ የቴሌቪዥን አገልግሎትን ከአናሎግ ወደ ዲጂታል ቴክኖሎጂ ለማሸጋገር በተቋቋመው አገር አቀፍ ኮሚቴ ውስጥ በመሳተፍ ሽግግሩን ለማከናወን የሚያስችል የተለያዩ ቅድመ ዝግጅት ስራዎችን ሰርቷል፡፡

JoomShaper