A- A A+

ቅሬታና ጥቆማ

User Rating: 1 / 5

Star ActiveStar InactiveStar InactiveStar InactiveStar Inactive
 

በብሮድካስት አገልግሎት ላይ የሚቀርቡ ጥቆማዎችና ቅሬታዎች

ጥቆማ፡- ባለስልጣን መ/ቤቱ ባወጣዉ የብሮድካስት አገልግሎት የቅሬታ ማስተናገጃ መመሪያ ቁጥር 03/2000 ላይ “ጥቆማ ማለት በማንኛዉም ብሮድካስተር ላይ የብሮድካስት አገልግሎትን አስመልክቶ ማስተካከያ ወይም እርምት እንዲደረግ ለባለስልጣኑ የሚቀርብ መረጃ የሚሰጥ አስተያየት ነዉ፡፡” የሚል ትርጓሜ ተሰጥቶታል፡፡

በትርጓሜው መነሻነት ጉዳዩን ግልጽ ለማድረግ ጥቆማ የሚቀርብባቸዉ ዋና ዋና ሃሳቦች የሚከተሉት ሲሆን ማንኛውም ጉዳዩ ይመለከተኛል የሚል አካል፡-

=> የድምጽና የምስል ጥራት መጓደል ሲያጋጥም

=> የሚዛናዊነት ችግር (ጉዳዩ ከሚመለከታቸዉ አካላት የአንድ ወገን ሃሳብ ብቻ በዜና ወይም በፕሮግራም ማካተት)

=> ማንኛዉም ለስርጭት የሚቀርብ ፕሮግራም፡-

  • ·      የሰዉ ልጆችን ስብዕናና ነጻነት ወይም ስነ ምግባር የሚጻረር ወይም የሌሎችን እምነት የሚያንኳስስ ከሆነ

·      በመንግስት ፀጥታ ወይም በሕገ መንግስቱ መሠረት በተቋቋመ የመንግስት አስተዳደር ወይም በአገር መከላከያ ኃይል ላይ የወንጀል ድርጊት የሚፈጽም ከሆነ

·      የግለሰብን፣ የብሔር ብሔረሰብን፣ የሕዝብን ወይም የድርጅትን ስም የሚያጠፋ ወይም በሐሰት የሚወነጅል ከሆነ

·      ጦርነት የሚቀሰቅስ ከሆነ

=>  የልጆችን አመለካከት፣ ስሜትና አስተሳሰብ ወደ አልተፈለገ አቅጣጫ እንዲያዘነብሉ የሚገፋፉ የሬዲዮና የቴሌቭዥን ሥርጭቶችን ልጆች ሊመለከቱት በሚችሉበት ሰዓት ከተላለፈ

=>  የሌላዉን ምርት ወይም አገልግሎት በማጥላላት ወይም በማንኳሰስ የሚቀርብ ማስታወቂያ

=>  የስርዓተ ጾታ እኩልነትን፣ የሴቶች ሰብአዊ መብትና ክብርን የሚያንኳስሱና የሚጋፉ ማናቸዉም ማስታወቂያዎች

=>  የሲጋራና ሲጋራ ነክ ማስታወቂያዎች ካጋጠሙ

=>  የአልኮል መጠናቸዉ ከ12 በመቶ በላይ የሆኑ መጠጦች ማስታወቂያ ካጋጠሙ

=>  ማናቸዉም ያለሐኪም ትዕዛዝ ሊሰጡ የማይችሉ መድኃኒቶችን በቀጥታ ተጠቃሚ እንዲገዛ የሚገፋፉ ማስታወቂያዎች ካጋጠሙ

እንዲሁም ማስተካከያ ያሻቸዋል ተብለዉ በሚገመቱ በብሮድካስት አገልግሎት በተሰራጩ ፕሮግራሞች ላይ ለባለስልጣኑ ጥቆማ መስጠት ይቻላል፡፡

ቅሬታ፡- የብሮድካስት አገልግሎት የቅሬታ ማስተናገጃ መመሪያ ቁጥር 03/2000 ላይ “ቅሬታ ማለት በብሮድካስት አገልግሎት በተላለፈ ፕሮግራም መብቴ ተነክቷል ወይም በአግባቡ አልተስተናገድኩም በማለት በብሮድካስተሮች ላይ የሚቀርብ አቤቱታ ነዉ፡፡” የሚል ትርጓሜ ተሰጥቶታል፡፡

በዚህ ሃሳብ ላይ በመመርኮዝ ከብሮድካስት አገልግሎት ጋር በተገናኘ የተሰራጨ ፕሮግራም፣ የድምጽ ወይም የምስል ጥራት፣ የሞገድ ጣልቃ ገብነትና የመሳሰሉትን አስመልክቶ መብቴ ተጥሷል፣ጥቅሜ ተነክቷል ወይም ጉዳት ደርሶብኛል በሚል ግለሰብ ወይም አካል ቅሬታ ሊቀርብ ይችላል፡፡

የጥቆማና ቅሬታ አቀራረብ

በብሮድካስት አገልግሎት በሚሰራጩ ፕሮግራሞች ላይ ማንኛዉም ዜጋ በአካል በመቅረብ፣ በፖስታ ቤት በመላክ፣ በባለስልጣኑ ኢሜል ወይም ካለበት ሆኖ ስልክ በመደወል ጥቆማዉን ለባለስልጣኑ ማቅረብ ይችላል፡፡

ቅሬታን ማቅረብ የሚቻለዉ በጽሑፍ ሆኖ ለዚሁ የተዘጋጀዉን  ቅጽ በመሙላት ነዉ፡፡ ቅጹም የቅሬታ አቅራቢዉን ስምና አድራሻ፣ ቅሬታ የቀረበበትን ብሮድካስተር ስም፣ የብሮድካስት አገልግሎቱ ዓይነት (ሬድዮ ወይም ቴሌቭዥን)፣ ለቅሬታዉ መነሻ የሆነዉ ድርጊት የተፈጸመበት ቀንና ሰዓት፣ የፕሮግራሙ ርዕስ፣ ለቅሬታዉ መነሻ የሆነዉ ድርጊት በቅሬታ አቅራቢዉ ላይ ያስከተለዉ የመብት ጥሰት ወይም ጉዳት፣ ለብሮድካስተሩ አስቀድሞ ቅሬታ ቀርቦ ከሆነ የተገኘዉ ዉጤት ወይም የተሰተዉ መልስ፣ ቅሬታዉ የሚቀርበዉ በወኪል ከሆነ የዉክልና ማስረጃ ከቅሬታ ማመልከቻ ጋር መያያዝ አለበት፡፡

የማጣራት ሂደት

የቀረበዉ ቅሬታ ተቀባይነት ያለዉ ከሆነ በበላይ ኃላፊ የተቋቋመዉ ቅሬታዎችን ተቀብሎ አጣርቶ ዉሳኔ የሚሰጥ ቅሬታ ሰሚ ቡድን አስፈላጊዉን መረጃና ማስረጃ በመሰብሰብ ቅሬታ የቀረበበትን ብሮድካስተር መልስ በመቀበል ጉዳዩን ያጣራል፡፡ ዉሳኔም በመስጠት ለቅሬታ አቅራቢዉና ቅሬታዉ ለቀረበበት ብሮድካስተር በጽሑፍ ያሳዉቃል፡፡ የዉሳኔዉንም ተግባራዊነት ይከታተላል፡፡

በዉሳኔዉ ላይ ያልተስማማ ቅሬታ አቅራቢ ወይም ብሮድካስተር ዉሳኔዉ በደረሰዉ በ14 ቀናት ዉስጥ ለመ/ቤቱ የስራ አመራር ቡድን ቅሬታ ማቅረብ ይችላል፡፡ የስራ አመራር ቡድኑ ቅሬታዉን መርምሮ ዉሳኔ ይሰጣል፡፡ በስራ አመራር ቡድኑ ዉሳኔ ቅር የተሰኘ ቅሬታ አቅራቢ ወይም ብሮድካስተር ዉሳኔ በደረሰዉ በ14 ቀናት ዉስጥ ለቦርዱ የይግባኝ ቅሬታ ማቅረብ ይችላል፡፡ ቦርዱም ቅሬታዉን መርምሮ የመጨረሻ ዉሳኔ ይሰጣል፡፡

የቅሬታ ማቅረቢያ ቅፅ ከየት ይገኛል?

በሬዲዮና ቴሌቪዥን ጣቢያዎች ላይ ቅሬታ ወይም ጥቆማ የሚያቀርብ ማንኛውም ሰው  ለዚህ ተብሎ የተዘጋጀውን የቅሬታና ጥቆማ ማቅረቢያ ቅፅ ከባለስልጣን መ/ቤቱ የመገናኛ ብዙኃን ክትትልና አቅም ግንባታ ዳይሬክቶሬት ቢሮ ቁጥር 403  በአካል በመቅረብ ወይም ከመ/ቤቱ ድረ ገፅ www.eba.gov.et ማግኘት ይችላሉ፡፡ በተጨማሪም ይህንን በመጫን በቀጥታ መላክ ይችላሉ፡፡

JoomShaper