የጥላቻ ንግግር እና የሐሰተኛ መረጃ ስርጭትን ለመከላከል ቅንጅታዊ አሰራርን ማጠናከር እንደሚያስፈልግ ተገለፀ
የጥላቻ ንግግር እና የሐሰተኛ መረጃ ስርጭትን ለመከላከል ቅንጅታዊ አሰራርን ማጠናከር እንደሚያስፈልግ ተገለፀ
በኢፌዲሪ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የዲሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ የተከበሩ አቶ እዉነቴ አለነ በሀገራችን የጥላቻ ንግግር እና የሐሰተኛ መረጃ ስርጭትን ለመከላከል ቅንጅታዊ አሰራርን ማጠናከር እንደሚያስፈልግ ተናገሩ።
የተከበሩ አቶ እዉነቴ አለነ ይህን ያሉት የዲሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የጥላቻ ንግግር እና የሐሰተኛ መረጃ ስርጭትን ለመከላከል ከኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን ጋር ውይይት ባደረጉበት ወቅት ነው፡፡
ሰብሳቢዉ አክለዉም የጥላቻ ንግግር እና ሐሰተኛ መረጃ ስርጭትን የመከላከል ስራ ለአንድ ተቋም ብቻ የተተወ ጉዳይ ባለመሆኑ የኮሚቴዉ አባላት ወደ ማህበረሰቡ ሲመለሱ የጥላቻ ንግግር እና የሐሰተኛ መረጃ ስርጭት በሚያስከትለዉ ጉዳት ዙሪያ የህብረተሰቡን ግንዛቤ ለማሳደግ በክረምት ስራቸዉ አንዱ አካል አድርገዉ መስራት እንደሚገባቸዉ አሳስበዋል።
የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር ክቡር አቶ መሐመድ እድሪስ በበኩላቸዉ የጥላቻ ንግግር እና ሐሰተኛ መረጃ ስርጭትን ለመግታት በሚደረገዉ ጥረት የቋሚ ኮሚቴዉ አባላት የሚያደርጉት ድጋፍና ተሳትፎ ወሳኝ ሚና አለዉ ብለዋል፡፡
ዋና ዳይሬክተሩ አክለዉም ባለሥልጣኑ የጥላቻ ንግግር እና የሐሰተኛ መረጃ ስርጭትን ለመከላል ከባለድርሻ አካላት ጋር ቅንጅታዊ አሰራር በመፍጠር የማህበረሰቡን ግንዛቤ የሚያሳድግ ሰፊ ስራ እያከናወነ መሆኑን ገልፀዋል፡፡
የቋሚ ኮሚቴዉ አባላት በበኩላቸዉ የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን በሀገር ላይ ፈተና የደቀነዉን የጥላቻ ንግግር እና የሐሰተኛ መረጃ ስርጭት ለመከላከል እያከናወነ ያለዉን ጥረት አድንቀዉ ወደ መረጣቸው ማህበረሰብ ሲመለሱ የጥላቻ ንግግርና የሐሰተኛ መረጃ እያስከተለ ያለውን ጉዳት በማስገንዘብ ስርጭቱን ለመግታት የበኩላቸውን እንደሚወጡ ተናግረዋል፡፡
በመጨረሻም ቋሚ ኮሚቴዉ ሁሉም የህብረተሰብ ክፍል በያገባኛል ስሜት የጥላቻ ንግግር እና የሐሰተኛ መረጃ ስርጭትን ለመከላከል የበኩሉን ድርሻ እንዲወጣ መልዕክት አስተላልፈዋል።