የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን በመሰረታዊ የጋዜጠኝነት ስነ-ምግባር እና ሚዲያ አጠቃቀም ክህሎት ላይ ያተኮረ ስልጠና በሃዋሳ ከተማ ሰጠ
የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን በመሰረታዊ የጋዜጠኝነት ስነ-ምግባር እና ሚዲያ አጠቃቀም ክህሎት ላይ ያተኮረ ስልጠና በሃዋሳ ከተማ ሰጠ
የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን ከተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ለተውጣጡ ሰልጣኞች በመሰረታዊ የጋዜጠኝነት ስነ-ምግባር እና መርሆዎች፣ በሃቅ ማጣሪያ መንገዶች እና በሚዲያ አጠቃቀም ክህሎት ዙሪያ በሃዋሳ ከተማ ሰልጠና ሰጥቷል፡፡
በሰልጠናው ላይ ተገኝተው የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን የስትራቴጂክ ጉዳዮችና የአቅም ግንባታ መሪ ስራ አስፈጻሚ አቶ ታምራት ደጀኔ የስልጠናው ዋና ዓላማ ሰልጣኞች በመሰረታዊ ጋዜጠኝነት ስነ-ምግባር እና መርሆዎች፣ በሃ ቅ ማጣሪያ መንገዶች ላይ ግንዛቤያቸውን በማሳደግ እና ኃላፊነትን የተላበሰ የሚዲያ አጠቃቀም ክህሎት በማዳበር በዘርፉ የሚስተዋሉ ችግሮችን በመቅረፍ ራሳቸዉን ብሎም ሀገራቸዉን ከተዛቡ መረጃዎች እንዲጠብቁ ለማስቻል ያለመ ነው ብለዋል፡፡
አቶ ታምራት አክለውም የሚዲያ ኮሙኒኬሽን የቴክኖሎጂ እድገት ለማንኛውም የስራ ሂደት መቀላጠፍ ጉልህ አስተዋፅኦ ቢኖረውም በአግባቡ ካልተጠቀሙበት ለጥላቻ ንግግርና ሐሰተኛ መረጃ ከፍተኛ ሚና ስለሚኖረው ዜጎች እጃቸው ላይ ያለውን ቴክኖሎጂ በአግባቡ ሊጠቀሙበት እንደሚገባ ገልፀው በስልጠናው ላይ የተሳተፉ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ከስልጠናው ያገኙትን እውቀት ለሌሎች ማካፍል እንደሚጠበቅባቸውም አሳስበዋል።
የደቡብ ሬዲዮና ቴሌቪዥን ድርጅት ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ ዘላለም ገነሞ በበኩላቸው የጋዜጠኝነት ሙያ በአግባቡ ከተጠቀሙበት ሀገርን የሚያለማ፣ ማህበረሰቡን በመረጃ የሚያበለፅግና የሚያዘምን እንዲሁም የዜጎችን የዴሞክራሲ ባህልና ልምምድ የሚያጎለብት የልማት አንቀሳቃሽ ሞተር ነው። ሙያውን በአግባቡ ካልተጠቀምን ደግሞ ማህበረሰቡን እርስበርስ በማቃቃር፣ በማጠራጠር ለሠላም መደፍረስ ዋነኛው ምክንያት በመሆን ከሀገር ግንባታ ይልቅ ሀገር የማፍረስ ሚናው ከፍተኛ መሆኑን በመረዳት ሙያውን በከፍተኛ ጥንቃቄ መጠቀም ይገባል ብለዋል።
ሰልጣኞች በበኩላቸው ስልጠናው በጋዜጠኝነት ስነ-ምግባር እና መርሆች እንዲሁም በሚዲያ አጠቃቀም እና ሃቅ ማጣሪያ መንገዶች ዙሪያ ግንዛቤ እንደፈጠረላቸው ገልፀው የጥላቻ ንግግርና የሐሰተኛ መረጃ ስርጭትን ለመግታት በሚደረገው ሂደት ትክክለኛነታቸው ያልተረጋገጡ መረጃዎችን ከማሰራጨትና ከማጋራት ተቆጥበን የሚያሰራጩትን እና የሚያጋሩትንም ጥቆማ በመስጠት ከባለሥልጣኑ እና ሌሎች ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በትብብር በመስራት የበኩላቸውን እንደሚወጡ ተናግረዋል፡፡
በመጨረሻም በጋዜጠኝነት ስነ-ምግባር እና መርሆዎች እንዲሁም በሚዲያ አጠቃቀም እና በሃቅ ማጣሪያ መንገዶች ዙሪያ ስልጠናዉን ለተካፈሉ ሰልጣኞች በኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር ፅ/ቤት ኃላፊ ወ/ሮ የሽወርቅ ግርማ ስርተፍኬት ተበርክቶላቸዋል፡፡
የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን በመገናኛ ብዙኃን ዘርፍ የዜጎችን ተሳትፎ እና የሚዲያ አጠቃቀም ክህሎት /Media literacy/ የሚያሳድጉ ዘዴዎችን ቀይሶ ዜጎች ራሳቸዉን፣ ቤተሰባቸዉን ብሎም ሀገራቸዉን ከሐሰተኛ መረጃ እንዲከላከሉ ለማስቻል የሚያግዙ ስልጠናዎችን ለተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች እየሰጠ እንደሚገኝ ይታወቃል፡፡