የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣንና የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር በጋራ በሚሰሩባቸው ጉዳዮች ዙሪያ የስምምነት ሰነድ ተፈራረሙ
የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣንና የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር በጋራ በሚሰሩባቸው ጉዳዮች ዙሪያ የስምምነት ሰነድ ተፈራረሙ
የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣንና የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ልዩ ትኩረት የሚሹ የህብረተሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ ሊያደርጉ በሚችሉ ጉዳዮች ዙሪያ በጋራ ለመስራት የስምምነት ሰነድ ተፈራርመዋል።
የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ሚኒስትር ኤርጎጌ ተስፋዬ (ዶ/ር) የመድረኩ ዋነኛ ዓላማ እንደ ሀገር ልዩ ትኩረት የሚሹ የህብረተሰብ ክፍሎችን መብት ለማክበርና አካታች በሆነ መልኩ ተጠቃሚነታቸውን ለማስጠበቅ መገናኛ ብዙኃን በትኩረት መስራት እንዳለባቸው ለማሳየት፣ የህብረተሰቡን የተዛባ አመለካከት በትብብር ለመለወጥና ጉዳዮ በሁሉም ማህበረሰብ ዘንድ ልዮ ትኩረት እንዲፈጥር ለማድረግ መሆኑን ገልጸዋል።
መገናኛ ብዙኃን የሚጠበቅባቸውን ሚና በአግባቡ ለመወጣት ከሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ጋር በቅርበት እና በቅንጅት ሊሰሩ እንደሚገባ ሚኒስትሯ አክለው ገልጸዋል፡፡
የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን ም/ ዋና ዳይሬክተር አቶ ግዛው ተስፋዬ በበኩላቸው፤ ልዩ ትኩረት የሚሹ የህብረተሰብ ክፍሎችን የልማት ተሳታፊነት፣ ፍትሃዊ ተጠቃሚነትና ተዛማጅ ጉዳዮች ዙሪያ ከመገናኛ ብዙኃን ጋር ያለውን ግንኙነትና ቅንጅታዊ አሰራር ለማጠናከርና የጋራ ማህበራዊ ሃላፊነትን ለመወጣት የሚያስችል ግንዛቤ ለመፍጠር የአሰራር ስርዓት መዘርጋት እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል።
በመድረኩ ላይ ልዩ ትኩረት የሚሹ የህብረተሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ ለማድረግ የመገናኛ ብዙኃን ሚናን በተመለከተ ከመገናኛ ብዙኃን ኃላፊዎች እና ባለሙያዎች የጋራ ግንዛቤ ለማስጨበጥ የሚረዱ ሰነዶች ቀርበው ውይይት ከተደረገባቸው በኋላ ከመገናኛ ብዙኃን ጋር በትብብር ለመስራት የሚዲያ የጋራ ፎረም ተመስርቷል።