ስለ ባለስልጣኑ
የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን
የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን በአዋጅ ቁጥር 1238/2013 የተቋቋመ የፌዴራል መ/ቤት ሲሆን ተጠሪነቱ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ነው። ባለሥልጣኑ በመገናኛ ብዙኃን አዋጅ ቁጥር 1238/2013 መሠረት መገናኛ ብዙኃንና የማስታወቂያ ዘርፍን በአጠቃላይ እንዲከታተል እና እንዲደግፍ ሆኖ ተቋቁሟል።
በመገናኛ ብዙኃን አዋጅ መሠረት የባለሥልጣኑ ዓላማ በኢትዮጵያ ፌደራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፖብሊክ ሕገ መንግሥትና በኢትዮጵያ ላይ ግዴታ በሚጥሉ ዓለም አቀፋዊ የሰብዓዊ መብት ስምምነቶች የተረጋገጠውን ሀሳብ በነፃነት የመግለፅና የመገናኛ ብዙኃን ነፃነትን በተሟላ መልኩ እንዲረጋገጥ የሚያስችሉ ምቹ ሁኔታዎችን መፍጠር፤ መገናኛ ብዙኃን ተግባራቸውን በሕጉ መሠረት ማከናወናቸውን ለማረጋገጥ፣ ክትትልና ቁጥጥር ማድረግ፤ የመገናኛ ብዙኃን የእርስ በእርስ ቁጥጥርና ግምገማ እንዲጠናከር ተገቢውን ድጋፍ መስጠት፤ በብሮድካስት አገልግሎት ፈቃድ መስጥት፣ የአገልግሎት ተጠቃሚነት፣ ባለቤትነት፣ዝግጅትና ሥርጭት ላይ ብዝኃነት እንዲጠበቅና እንዲስፋፋ መሥራት እንዲሁም የመገናኛ ብዙኃን ዘርፍ ባለድረሻ አካላት በመደበኛነት የሚወያዩበት መድረክ ማመቻቸት፣በመገናኛ ብዙኃንና በመንግሥት አካላት መካከል መልካም የሥራ ግንኙነት እንዲኖርና እንዲጠናከር የሚያስችሉ ተግባራትን ያከናውናል፡፡
ባለሥልጣኑ የብሮድካስት፣ የህትመት እና የበየነመረብ መገናኛ ብዙኃንን ይመዘግባል፣ ፍቃድ ይሰጣል እንዲሁም የክትትል ስራ ይሰራል። በተጨማሪም ከሌሎች ተቋማት ጋር በመቀናጀት የጥላቻ ንግግርና የሐሰተኛ መረጃ ስርጭትን ለመከላከል እና ለመቆጣጠር የወጣውን አዋጅ እና የማስታወቂያ አዋጅን ያስፈፅማል፡፡
የመገናኛ ብዙኃንን ከመቆጣጠር ባለፈ የዘርፉን ሙያዊ ብቃት ለማሳደግ እና የይዘት ብዝኃነት እንዲኖር በዘርፉ ላይ ጥናትና ምርምር በማድረግ የአቅም ግንባታ ስራ ይሰራል፣ የሚዲያ ፖሊሲ መነሻ ሃሳቦችን ያመነጫል፡፡
Asset Publisher
የቴክኒክና ሙያ ስልጠና ለሀገር ሁለንተናዊ ዕድገት አዎንታዊ አስተዋፅኦ እንዲያበረክት መገናኛ ብዙኃን የበኩላቸውን ሚና ሊወጡ እንደሚገባ ተጠቆመ፡፡
የቴክኒክና ሙያ ስልጠና ለሀገር ሁለንተናዊ ዕድገት አስተዋፅኦ እንዲያበረክት መገናኛ ብዙኃን የበኩላቸውን ሚና ሊወጡ እንደሚገባ "ክህሎት ለሁለንተናዊ ስኬት" በሚል መሪ ሀሳብ ለመገናኛ ብዙኃን አመራሮችና ባለሙያዎች በተዘጋጀ የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረክ ላይ ተጠቆመ፡፡
በመድረኩ ላይ የተገኙት የስራና ክህሎት ሚኒስቴር ሚኒስትር ወ/ሮ ሙፋሪያት ከማል እንዳሉት የቴክኒክና ሙያ ስልጠና ለማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ እድገት መሰረት እንደሆነ ይታወቃል፡፡ በሀገራችን ተጨባጭ ሁኔታ ግን ዘርፉ እንደ አማራጭ የትምህርትና ሥልጠና ስርዓት ሳይሆን በቀለም ትምህርት መግፋት ያልቻሉ ብቻ የሚገቡበት ሆኖ ይታያል፡፡ በአዲሱ የትምህርትና ሥልጠና ፖሊሲ ዘርፉ አማራጭ ያጡ ሳይሆን መርጠው የሚገቡበት መስክ እንዲሆን መንግስት በርካታ ስራዎችን እየሰራ ይገኛል፡፡ ይህን የለውጥ ሀሳብ በአግባቡ ተደራሽ ማድረግ የሚቻለው ደግሞ በመገናኛ ብዙኃን በኩል በመሆኑ ለሚዲያ አመራርና ባለሙያዎች ተገቢውን ግንዛቤ መፍጠር ያስፈልጋል፡፡
መገናኛ ብዙኃን የቴክኒክና ሙያ ስልጠና ስርዓቱ ላይ ያሉ መሰረታዊ የለውጥ አቅጣጫዎችና ከሀገራዊ የፖሊሲ አቅጣጫዎች ጋር ያላቸው አንድምታ ላይ ግንዛቤያቸውን በማሳደግ ስለቴክኒክና ሙያ ስልጠና በህብረተሰቡ ዘንድ ያለውን አሉታዊ አስተሳሰብ የሚቀይሩና የባህሪ ለውጥ የሚያመጡ ዜናና ፕሮግራዎችን አቅደው በመስራት የበኩላቸውን ሚና ሊወጡ እንደሚገባም ሚኒስትሯ ጨምረው ተናግረዋል።
በመድረኩ አስተያየት የሰጡ የመገናኛ ብዙኃን ኃላፊዎችና ባለሙያዎች ባገኙት ግንዛቤ ተመስርተው በዜናና ፕሮግራሞቻቸው ላይ በማካተት ሰፊ ስራ መስራት እንደሚጠበቅባቸው ተናግረዎል።
መድረኩን የስራና ክህሎት ሚኒስቴር ከፌደራል ቴክኒክና ሙያ ኢኒስቲትዩት፣ ከመገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን እና ከዋልታ ሚዲያ እና ኮሙዩኒኬሽን ኮርፖሬት ጋር በመተባበር መዘጋጀቱ ተመላክቷል።