ኢ.መ.ብ.ባ ሁለተኛ ዙር ለመከላከያ ሠራዊት የደም ልገሳ መርሐግብር አካሄደ
ህዳር 27 2014 ዓ.ም
የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎችና ሰራተኞች “ደማችንን ለመከላከያ ሰራዊታችን” በሚል መሪ ቃል ለሁለተኛ ዙር ለመከላከያ ሠራዊት የደም ልገሳ መርሐግብር አካሄዱ።
መርሐግብሩ ከፌደራል ዋና ኦዲተር መስሪያ ቤት ጋር በጋራ በመሆን የተከናወነ ሲሆን ባለሥልጣን መስሪያ ቤቱ ከተሰጠው ተልዕኮ በተጨማሪ በሀገራዊ ጉዳዮች ላይ ይሳተፋል።
የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ዮናታን ተስፋዬ በመከላከያ ሰራዊት ላይ የተጋረጠውን የህልውና ዘመቻ ለመቀልበስ በሚደረገው ትግል እያገኘናቸው ያሉት ድሎች በቀላሉ የተገኙ አይደሉም፤ ከፍተኛ የደም መስዋዕትነት ተከፍሎባቸዋል። ስለዚህ የመገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎችና ሰራተኞች ደም በመለገስ የበኩላቸውን አስተዋፅኦ እያደረጉ መሆኑን ገልፀዋል።
በተመሳሳይ የፌደራል ዋና ኦዲተር መ/ቤት የኦዲት ዘርፍ ምክትል ዋና ኦዲተር ወ/ሮ መሠረት ዳምጤ በመርሐግብሩ ላይ መከላከያ ሰራዊታችን በትግል ላይ ነው። ስለዚህ ሀገራችንን ከገባችበት ችግር ለማውጣት ዛሬ ብቻ ሳይሆን ድጋፋችንን ለወደፊቱም አጠናክረን እንቀጥላለን ብለዋል።
ባለሥልጣን መስሪያ ቤቱ ከዚህ ቀደም ለመከላከያ ሰራዊት የወርሃዊ ደሞዝ ልገሳ ያደረገ ሲሆን “ለአገር መከላከያ ሰራዊታችን ክብር እሮጣለሁ” በሚል መሪ ቃል የስፖርት ኮሚሽን ባዘጋጀው የሩጫ ውድድር ላይ በመሳተፍም ከሰራዊቱ ጎን መሆኑን አሳይቷል።